“እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም።” (ገላትያ 1፥7)
“ክርስቲያናዊ ሕይወት በሙሉ መመዘን ያለበት በቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ነው።” — ጆን ዊክሊፍ
በዚህ አነስተኛ የጽሑፍ ዐውድ፣ “ኦርቶዶክስ” የሚለው ቃል አግባብነት፣ የማከብራትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ለማመልከት አይደለም። ከሥርወ ቃላት ትንተና (etymology) አንጻር የቃሉን መሠረታዊ ፍቺ ለማሳየት የዋለ ነው። “ኦርቶዶክስ” (ὀρθόδοξος)፣ መንታ ቃል ነው፤ አንደኛው “ኦርቶስ (ὀρθός)” — ቀጥተኛ፣ ትክክል፣ ያልተበረዘ የሚሉ ዐሳቦችን የያዘ፣ ሲሆን ሁለተኛው “ዶክሳ (δόξα)”፣ አስተምህሮና አመለካከትን የሚገልጽ ነው። በዚህ መሠረት “ኦርቶዶክስ” ስንል፣ “ቀጥተኛ፣ ትክክል፣ ያልዘመመ” መሠረት ላይ ያረፈ እምነት ማለታችን ነው። ከክርስትና እምነት አንጻር የእምነታችን ትክክለኛነት ቱንቢና የመጨረሻው ባለሥልጣን ቅዱስ ቃሉ ነው!
የቤተ ክርስቲያን የተልእኮ እንዳለችበት ዘመንና ትውልድ ዐውዳዊ ነው። ሆኖም ማንነቷና የወንጌል መልእክቷ ግን አይቀየሩም። የቤተ ክርቲስቲያን ዐውዳዊነት በየጊዜው በቅዱስ ቃሉ ብርሃን ፍተሻና ቅኝት ያስፈልገዋል ማለት ነው። የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ዐውዳዊ ነው ስንል፣ ትውልዱ ባለበት ዐውድ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛ አዳኝነትና ጌትነት መስበከ ማለት ነው። ሳይጨመር፤ ሳይቀነስ፤ ሳይበረዝ። የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ክፍት፣ ገደብ የለሽና ሁሉን ዐቃፊ አይደለም። የስብከቷ ዋልታና ማገር ክርስቶስና ሥራው ብቻ ነው ነው። የሰው አካል ያለ ልብ እንደማይኖር ሁሉ፣ የቤተ ክርስቲያንም ማንነት ያለ ክርስቶስ ወንጌል ምውት ነው።
ማንኛውም ክርስቲያናዊ ትውልድ ከእርሱ ቀደም ሲሉ ወይም ከተከታይ ትውልዶች ጋር የዐውድ መጋጠሚያና መለያያ ቢኖረውም፣ በቅዱስ ቃሉ ላይ ያለው የወንጌል መልእክት ግን ቋሚና የማይበጠስ አያያዥ ሰንሰለት ነው። ሁሉም ትውልድ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ለወንጌል ታማኝ እንዲሆን ተጠርቷል። በአብዮተኝነት መንፈስ የቀደመውን ትውልድ ተልእኮአዊ የራስ ግንዛቤና እንቅስቃሴ አናፈርስም፤ በዚያኑ ልክ ለራሳችን ዐውድ አግባብነት ባለው መልኩ ወንጌል በታማኝ ልንሰብክ ያስፈልጋል። ክርስቶስ፣ ሕይወቱና የቤዝዎት ሥራው ለሁሉም ትውልድ የሚሆን ዘላለማዊ ነው። አግባብነቱ ሁልጊዜ ሕያው ነው።
እንደማስተውለው፣ ትልቁ ቀውስ “ዐውድ” በራሱ መልዕክት ሆኖ የወንጌልን ሥፍራ ሲወስድ ነው። ቤተ ክርስቲያንን “አግባብነትና ተቀባይነት” ለማግኘት ስትል ከባህል፣ ከታሪክ፣ ከማኅበራዊ ጕዳዮችና ከፓለቲካ ጋር ድንበር የለሽ ዝምድና ስትፈጠር የክርስቶስን ወንጌል አንጻራዊ ማድረጓ አይቀርም። የኢትዮጵያ ወንጌላዊ ክርስትና የወቅቱ የማንነትና የተልዕኮ ቀውስ የዚህ ጤና የጐደለው ዝምድና ውጤት ይመስለኛል።
የወንጌላዊ ሚሲዮናዊ ማእከል የነበረው የምዕራቡ ዓለም አሁን የደረሰበትን የድኅረ-ክርስትና የአመራር፣ መንፈሳዊና ሥነ-ምግባራዊ ቀውሶች የቁልቁሎሽ መንገድ የሄደው በዝጋታ ሶምሶማ ነበር ። ቢያንስ በስኮትላንድ የዛሬ መቶ ዐሥር ዓመት የነበረውን ወርቃማ ዓለም ዐቀፋዊ የወጌል አጀንዳ መነሻ ካዳረግን (The 1910 World Missionary Conference, Edinburgh, 14–23 June, 1910)፣ የእኛን የወቅቱን ሁሉን ዐቃፊ የአስተምህሮና አመራር ቀውስ ስመለከት በፈጣን ሩጫ የገባንበት ይመስለኛል። የአመራር፣ የአስተምህሮ፣ የሞራልና የፋይናንስ ተጠያቂነት የሌለበትና እንደ ዘመነ መሳፍንት “እያንዳንዱም ሰው መልካም መስሎ የታየውን” የሚያደርግበት ዘመን ውስጥ ገብተናል። (መሳፍንት 21፥25)። መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ የጋራ ድምፅ ያጣንበት፣ የቤቱ ባለቤትና ራስ የሆነው ክርስቶስ ባይተዋር የሆነበት ይህን ዘመን እንዲታደስ ወደ ቃሉ እውነት ልንመለስ ይገባናል።
የቤተ ክርስቲያን መልእክት የተሰቀለው፣ የሞተው፣ የተነሣው፣ አሁን በአብ ዘንድ የተቀመጠውና በክብር ዳግመኛ የሚመለሰው ክርስቶስ ብቻ ነው። (1ቆሮ 1፥23)። እርሱ እኩያ፣ አናሳ፣ ተፎካካሪ ወይም ረዳት አምላክ የለውም። የስብከታችን ቅቡልነት፣ ተኣማኒነት እንዲሁም የጽድቅ ተጽእኖ ዐቅማችን መሠረቱ ያረፈው፣ ለእግዚአብሔር ቃል የመጨረሻና የበላይ ባለሥልጣንነት ባለን መሠጠትና ታማኝነት ላይ ነው። አማኙ ማኅበረሰብ ከጨለማ ወደ ሚደነቅ ብርሃኑ የተጠራ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ከሆነ (1ጴጥ 2፥9)፣ ይህን መሠረታዊ እምነት ከሚያፋልስ የትኛውም አስተምህሮ፣ ሃይማኖትና ርዕዮተ ዓለም ጋር የማይታረቅ ልይነት አለው።
ቃል ሥጋ ሆነ! በእርግጥ አምላክ እንደ እኛ ሆነ። የሰውን ሁለተና፣ በሥጋ ብቻ ሳይሆን በጊዜ፣ በቦታ፣ በቋናቋና ባህል ሰው ሆኗል። የእርሱ ቤዛዊ የመስቀል ሥራ በኀጢአት የተለወሰውን የሰውን ሁለነትና ዋጅቷል። ይህም ባህላችንን ያካተተ ነው። በእርግጥ በክርስቶስ ብቸኛ የማዳን ሥራ ከተዋጀን፣ ከወንጌል እውነት ጋር ከሚጣረሱ ፋይዳዎች ጋር ቀጥታ የሆነ የማይታረቅ ግጭት አለን። ቋንቋና ባህል የለሽ (culture-less) ክርስትና የለም። በአጭሩ፣ ክርስቲያናዊ መስተጋብሮች ከቋንቋና ባህል ጋር ሊለያዩ አይችሉም። ክርስቶስም በደሙ የዋጀንና የእግዚአብሔር መንግሥትና ካህናት ያደረገን “ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ” ነው።
ስለዚህ የክርስቶስ ብቸኛ ቤዛዊ ሥራ ዋጅቶና ስንል፣ ከኀጢአትና ባዕድ አምልኮ ጋር ትሥሥር ካለው ከየትኛው ባህልም ነው። ባህል ስንል — የማኅበራዊ ስብስባችን የጋራ ፋይዳ ነው። ይህም እምነታችንን፣ እሴቶቻችን፣ ቋንቋችንን፣ ርእዮተ ዓለማችንን፣ ሙዚቃ፣ ምግብ፣ ጋብቻ፣ የወንድ፣ የሴት የልጆች አንዲሁም ቤተ ሰባዊ ድርሻና ኀላፊነቶች በሙሉ ያጠቃለለ ማንነት ነው። ክርስቶስ በእነዚህ ፋይዳዎች ላይ ደባል ሆኖ አይደለም ያዳነን! ይልቁንም የእርሱ ሕዝብ ያደረገን፣ እነዚህን ማንነቶች ሁሉ በመለወጥ በእርሱ ውስጥ በተገኘው ማንነት ለክብሩ እንድንኖርለት ነው። በአንድ ጊዜ ለክርስቶስም ከወንጌል ጋር ተቃርኖ ላለውም ባህል መኖር አንችልም!
በዚህ አግባብነት የኦሮሚያው እሬቻ፣ የሲዳማው ፍቼ ጨምበላላ፣ የወላይታው ጊፋታ፣ የሀዲያው ያሆዴ እንዲሁም ተመሳሳይ ሌሎች ክልሎች ያሉ በዓላት ባህላዊ ብቻ ሳይሆን ሃማኖታዊ (ቢያንስ መንፈሳዊ) ገጽታም አላቸው። በየትኛውም መልኩ (ቢያንስ እንደ ወንጌላዊያን አማኞች) ኅሊናችን ላይ ጫና ሳናደርግ፣ ሁለቱን መለያያት አንችልም። አገራችን ውስጥ የተቻችሎ መኖርን ዕሳቤ እስካላናጋና የዐመፅና የመለያየት ምክንያት እስካልሆነ ድረስ፣ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ሕዝብ ያሻውን እምነትና ባህል የመከተል ነጻ ፈቃድና መብት አለው። ይህ ከሰብአዊ መብት ነው፤ ሕዝብም፣ መንግሥትም ሊያከብረው ይገባል።
ሆኖም ሁለት የአተያይ ተፋልሶዎችን አሉ። አንደኛውና ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ፣ ባህላዊ በዓላት ፈጽሞውኑ ሃይማኖታዊ ገጽታ የላቸውም የሚለው ደምሳሽ ሙግት ነው። ሁለተኛውና ጠበብ ባለ መልኩ ደግሞ ሲታይ፣ እነዚህ ባህላዊ በዓላት ከወንጌል እውነት ጋር ምንም ዐይነት ተቃርኖ የላቸውም የሚለው ክርስቲያናዊ ፋይዳ ነው።
ከእነዚህ ተፋልሶዎች የሚቀዱና ኀላፊነት የጐደላቸው ሦስት ጠረዝ ላይ የቆሙ ምልከታዎች አሉ።
አንደኛው፣ የትርክት እስረኛ በመሆንና ባህላዊ በዓላትን ፖለቲካዊ ልብስ በማልበስ፣ አገራችን ያለችበትን የክፍፍል ውጥረት የበለጠ የሚያከር ምልከታ ነው። ይኽ አስከፊ ጦስ አለው ነው። የአግላይነትና የጥላቻ ዑደት ውስጥ የበለጠ ይዘፍቀናል። ለትውልድ ይህን ልናወርስ አይገባም!
ሁለተኛው ምልከታ፣ በዓላትን ከባህል አንጻር ብቻ በማየት ክርስቲያናዊ ልብሰ ተክህኖ ለመስጠት የሚሞክር አመለካክት ነው።
ሦስተኛውና የመጨረሻው፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የታቀፉና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያሌላቸው ትውፊቶችን፣ ገድላትና ድርሳናትን በመንተራስ፣ ባህላዊ በዓላት በወንጌላዊ ክርስትና ዘንድ ቅቡለነት እንዲያገኙ የሚደረግ ሙግት ነው። በርግጥ ኦርቶዶክስም እኛን በበላይነት የሚዳኘን መጽሐፍ ቅዱስ ነው ካልን፣ ይህ ንጽጽር ተጣራሽ ነው።
ከኦርቶዶክስ ጋር በቀና ልብ፣ በጸሎትና በፍቅርና በበሰለ መጸሐፍ ቅዱሳዊ አመክንዮ መወያየት የላቀው መንገድ ሆኖ ሳል፣ ደግሞም የማይታረቁ ልዩነቶችን ያለጥላቻ በልበ ስፋት መቀበል ሲቻል፣ አንዳንድ ጠርዝ ላይ የቆሙ ዕይታዎች ቤተ ክርስቲያኒቷን ክብረ-ነክ በሆነ መልኩ እስከ ማንጓጠጥ መድረሳቸው ከወንጌላዊ ክርስትና ምግባር ጋር ተቃራኒ ነው። በዚያኑ አንጻርና ከብዙ አክብሮት ጋር፣ ወድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ እጅግ ለዘገዩት የቅይጥነት (syncretism)፣ ገድላት፣ ተኣምረት፣ ፍካርያት፣ ድርሳናት ወዘተ ውዝግቦች፣ መጸሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ምላሽ መስጠት ያሻታል። በተለይም እውነቱን የሚያውቁ የነገረ-መለኮት ሊቃውንት በጌታ ዘንድ ተጠያቂነት ያለበት ዐደራ አለባቸው።
የእኔ ትኩረት ሁለተኛው ምልከታ ላይ ያተኮረ ነው። ምክንያቱም ይህ አመለካከት፣ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የወንጌል አደባባዮች የምዕራቡን ዓለም ክርስትና ሕይወት ለነሣው ብዝኀተ-ሃይማኖተኝነት (religious pluralism) አሳልፎ ስለሚሰጥ ነው። እንዳስተዋልኩት፣ ይህ አመለካከት ክርስትና ከባህልና ሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ሊኖረው የሚገባውን ጤናማና ሚዛናዊ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ነገረ-መለኮታዊ ዕይታ እያደበዘዘ ይገኛል።
በአማኑኤል ካንት ፍልስፍና ነፋስ ተጽእኖ፣ የወንጌል እምነቱን በነጻ/ልቅ ነገረ አስተምህሮ (liberal theology) የተካውና፣ ኬምብሪጅን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ ተቋማት ያስተማረው ጆን ሂክ፣ “ሁሉም ሃይማኖቶች የአንዱ መለኮታዊ እውነት ልዮ ልዩ የሆኑ አቻ መልሶች ናቸው” በማለት የዘራው ዘር፣ የምዕራቡን ዓለም የወንጌል እምነት ለመሸርሽር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። (An Interpretation of Religion: Human Response to the Transcendent፣ Basingstoke: Macmillan, 1989, 301)። “በፍጥረተ ሃይማኖት (religious world) ውስጥ፣ ክርስቶስ ወደ አንዱ አምላክ ከሚያመላክቱት የመገለጥ ከዋክብት መካከል አንዱ እንጂ፣ በራሱ በቸኛና ፍጹም ብርሃን አይደለም” በማለት ከሞገተ በኋላ፣ ክርስቶስን መካከለኛና ብቸኛ አዳኝ አድርጎ መስበክ፣ “ሃይማኖታዊ ኢምፔሪያሊዝም ነው”፣ በማለት ደምድሟል (Philosophy of Religion [Englewood: Prentice — Hall, 1983] 107ff)።
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አሁን ለደረሰበት የራስ ውድቀት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው፣ የወንጌልን ንጽሕና ያጠለሸ ልቅ ኢኪዩሚዝም (ecumenism) እንደሆነ ታሪክ ያስገነዝበናል። የካውንስሉ ሁሉን ዐቃፊነት (ሃይማኖት፣ ባህልና ፓለቲካ) መርኽ መሠረት ያደረገው “ዶክትሪን ይለያያል ፍቅር አንድ ያደርጋል” የሚለው ተቃርኖአዊ አመለካከት ነው። የዚህ ዐይነቱ ኢኪዩሚዝም መንፈስ ምድራችን ላይ ሰንኮፉን ለመጣል እያኮበከበ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። በክርስትናና በሌሎች ሃይማኖች መካከል ያሉትን የማይታረቁ ልዩነቶች አንጻራዊ በማድረግ ሁሉን ያገበሰበሰው ኢ-ሥላሴያዊ ዓለም ዐቀፋዊነት (Unitarian Universalism) እምነት ተረኛ ይሆናል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት የዓለም አብያተ ክርስቲያናንት ካውንስል በአምስተርዳም ሲመሠረት፣ አሁን የደረሰበት መንፈሳዊ ቀውስ ላይ እደረሳለሁ ብሎ አልነበረም።
አጋር መሪዎች፣ የወንጌል እውነት ሲቀየጥ መንፈስ ቅዱስ ይሸሸናል — ልብ እንበል! ይህን የምለው ከብዙ አክብሮትና ትሕትና ጋር ነው። የክርስቶስ ወንጌል ከደባል ጋር የማያኖረውና ሊፋቅ የማይችል ድንበር አለው። መጸሐፍ ቅዱሳዊው ክርስትና ዋጋ ያስከፍላል! ለትውልዱ ምን ይሆን እያስተላለፍን ያለነው?
“ጢሞቴዎስ ሆይ፣ በዐደራ የተቀበልኸውን ሁሉ ጠብቅ፤” (1ጢሞ. 6፥20)።
ጌታ ሆይ፣ “ወንጌልን ዐደራ ጠባቂም፣ ታማኝ አስተላላፊም አድርገን”። አሜን!