የፓስተር ሊንዳ ባልድዊን የ21 አመት አገልግሎት ማጠናቀቂያና ሽግግር
በቶሮንቶ የምትገኘውን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ላለፉት 21 ዓመታት የልጆችና የወጣቶች አገልግሎትን በታማኝነት፣ በሙሉ ትጋትና በግምባር ቀደምትነት ሲያገለግሉ የቆዩትን የፓስተር ሊንዳ የ21 አመት አገልግሎትን ማጠናቀቂያና ሽግግርን በተመለከተ የደመቀ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡ በዚህም መሠረት January 21,2024 በቤተክርስቲያኗ ልዩ የእራት ምሽትና የምስክርነት ጊዜ ተከናውኗል ። በምሽቱ ለፓስተር ሊንዳ ልዩ ልዩ ስጦታዎች የተበረከተ ሲሆን ስለአገልግሎታቸው ፍሬ በርካታ ምስክርነት ቀርቧል፡፡ ፓስተር ሊንዳም በእግዚአብሔር ምሪት ወደ አገልግሎቱ መግባታቸውን ጊዜውም ሲደርስ አሁንም በእግዚአብሔር ምሪት ለተተኪያቸው ማስረከባቸውን ገልፀዋል። በዝግጀቱ ላይ ከቤተክርስቲያኗ አገልጋዮችና አባላት በተጨማሪ ጥሪ የተደረገላቸው የቶሮንቶ ከተማ የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን አብያተክርስቲያናት ሕብረት መሪዎችና መጋቢዎች የተለያዩ እህት አብያተክርስቲያናት መሪዎች እንዲሁም ከፓስተር ሊንዳ ጋር ያገለገሉና ቤተሰብ የሆኑ የኪዊንስ ዌይ ቶሮንቶ ካቴድራል አባላት ተገኝተው ለበኣሉ ድምቀት ሰጥተዋል፡፡በምሽቱ ፕሮግራም ላይ የቤተክርሰቲያኗ ዋና መጋቢ ፓስተር/ዶር ኤፍሬም ላእከ ማርያም የፓስተር ሊንዳ ባልድዊንን የሕይወት ታሪክና አገልግሎት አስመልክቶ በፎቶግራፍ የተደገፈ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የቤተከርስቲያኗ የሽማግሌዎች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ድልነሳሁ ቸኮለ እንደዚሁ በቤተክርቲያኗ አባላት ስም የምስጋና ንግግር አድርገው የተዘጋጀውን ስጦታ አበርክተዋል፡፡ በመርሃግብሩ ላይ የነበረውን የቃልና የዝማሬ አገልግሎት ያበረከቱት ከሕጻንነት ዕድሜ ጀምረው በፓስተር ሊንዳ እየተማሩና እየተኮተኮቱ ያደጉ ወጣቶች ሲሆኑ በተለያዬ የዕድሜ ክልሉ ያሉ ልጆች በየተወካዮቻቸው አማካይነት ያቀረቡት ምስጋና በጣም ልብ የሚነካ አስደሳች ትዕይንት ነበር፡፡
የካናዳ የኢትጵያውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት በቶሮንቶ የተደረገው ይህ አስደናቂ ሽግግርና በተለይም ፓስተር ሊንዳ ባልድዊን ላለፉት 21 ዓመታት ያፈሯቸው ወጣቶች በቶሮንቶ ከተማ ብቻ ሳይሆን ወደፊት በመላው ካናዳ ከተሞች ተበትነው ለቤተክርስቲያን አጋዥ ኃይሎች እንደሚሆኑ በማመን በበዓሉ ላይ ተገኘተን የአበባ ስጦታና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈናል፡፡